የዮሐንስ ሦስተኛው ደብዳቤ 1:1-14

  • ሰላምታና ጸሎት (1-4)

  • ለጋይዮስ የቀረበ ምስጋና (5-8)

  • ‘የመሪነት ቦታ የሚፈልገው ዲዮጥራጢስ’ (9, 10)

  • ድሜጥሮስ በሚገባ ተመሥክሮለታል (11, 12)

  • ዮሐንስ የነበረው ዕቅድና የላከው ሰላምታ (13, 14)

 ከሽማግሌው፣ ከልብ ለምወደው ለተወዳጁ ጋይዮስ።  የተወደድክ ወንድም፣ አሁን በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለህ* ሁሉ፣ በሁሉም ነገር እንዲሳካልህና ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ እጸልያለሁ።  ወንድሞች መጥተው እውነትን አጥብቀህ እንደያዝክ ሲመሠክሩ በመስማቴ እጅግ ደስ ብሎኛልና፤ ደግሞም በእውነት ውስጥ እየተመላለስክ መሆኑ በጣም አስደስቶኛል።+  ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም።*+  የተወደድክ ወንድም፣ በግል ባታውቃቸውም እንኳ ለወንድሞች በምታደርገው ነገር ታማኝ መሆንህን እያሳየህ ነው።+  እነሱም በጉባኤው ፊት ስለ አንተ ፍቅር መሥክረዋል። እባክህ፣ አምላክ ደስ በሚሰኝበት ሁኔታ ሸኛቸው።+  ከአሕዛብ ምንም ሳይቀበሉ የወጡት ለስሙ ሲሉ ነውና።+  ስለዚህ በእውነት ውስጥ አብረን የምንሠራ እንሆን ዘንድ እንዲህ ላሉ ሰዎች የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ የማሳየት ግዴታ አለብን።+  ለጉባኤው የጻፍኩት ነገር ነበር፤ ሆኖም በመካከላቸው የመሪነት ቦታ መያዝ የሚፈልገው+ ዲዮጥራጢስ ከእኛ በአክብሮት የሚቀበለው ምንም ነገር የለም።+ 10  በመሆኑም እኔ ከመጣሁ ስለ እኛ መጥፎ ወሬ በማናፈስ* የሚሠራውን ሥራ ይፋ አወጣለሁ።+ ይህም አልበቃ ብሎት ወንድሞችን በአክብሮት አይቀበልም፤+ እነሱን መቀበል የሚፈልጉትንም ለመከልከልና ከጉባኤ ለማባረር ይጥራል። 11  ወዳጄ ሆይ፣ መጥፎ የሆነውን አትከተል፤ ይልቁንም ጥሩ የሆነውን ተከተል።+ መልካም የሚያደርግ የአምላክ ወገን ነው።+ መጥፎ የሚያደርግ አምላክን አላየውም።*+ 12  ሁሉም ወንድሞች ስለ ድሜጥሮስ በሚገባ መሥክረዋል፤ እውነት ራሱም ይህን አረጋግጧል። እንዲያውም እኛም ጭምር ስለ እሱ እየመሠከርን ነው፤ የምንሰጠው ምሥክርነት ደግሞ እውነት እንደሆነ ታውቃለህ። 13  ብዙ የምነግርህ ነገር ነበረኝ፤ ሆኖም ከዚህ በላይ በብዕርና በቀለም ልጽፍልህ አልፈልግም። 14  ከዚህ ይልቅ በቅርቡ እንደማይህ ተስፋ አደርጋለሁ፤ በዚያን ጊዜ ፊት ለፊት እንነጋገራለን። ሰላም ለአንተ ይሁን። ወዳጆች ሰላምታ ያቀርቡልሃል። በግለሰብ ደረጃ ሰላምታዬን ለወዳጆች አቅርብልኝ።

የግርጌ ማስታወሻ

ወይም “ነፍስህ በመልካም ሁኔታ ላይ እንዳለች።”
“አመስጋኝ እንድሆን የሚያደርገኝ ነገር የለም” ማለትም ሊሆን ይችላል።
ቃል በቃል “ስለ እኛ ክፉ ቃላት በመለፍለፍ።”
አላወቀውም ማለት ነው።