የሕይወት ታሪክ

መስማት የተሳነኝ መሆኔ ሌሎችን ከማስተማር አላገደኝም

መስማት የተሳነኝ መሆኔ ሌሎችን ከማስተማር አላገደኝም

የተጠመቅኩት በ1941 የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። ይሁንና እስከ 1946 ድረስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በደንብ አልገባኝም ነበር። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? እስቲ ታሪኬን ላውጋችሁ።

በ1910ዎቹ ወላጆቼ ከተብሊሲ፣ ጆርጂያ ወደ ካናዳ ተዛወሩ፤ የሚኖሩት በምዕራባዊ ካናዳ፣ በሳስካችዋን ግዛት በምትገኘው በፔሊ ከተማ አቅራቢያ ባለ አንድ ትንሽ የእርሻ ቦታ ላይ ነበር። እኔ የተወለድኩት በ1928 ሲሆን ከስድስት ልጆች መካከል የመጨረሻው ነኝ። ከመወለዴ ስድስት ወራት አስቀድሞ አባቴ ሞተ፤ እናቴም ገና ሕፃን እያለሁ አረፈች። ብዙም ሳይቆይ ደግሞ ታላቅ እህታችን ሉሲ በ17 ዓመቷ ሞተች። በመሆኑም አጎቴ ኒክ፣ እኔን እንዲሁም ወንድሞቼንና እህቶቼን ወደ ቤቱ ወሰደን።

ትንሽ ልጅ እያለሁ አንድ ቀን በእርሻችን ላይ የሚገኝን አንድ ፈረስ ጭራ ስጎትት ቤተሰቦቼ አዩኝ። ፈረሱ እንዳይረግጠኝ ስለፈሩ ጮክ ብለው በመጣራት ጭራውን መጎተቴን እንዳቆም ነገሩኝ፤ እኔ ግን መጎተቴን አላቆምኩም። የሚጣሩት ከኋላዬ ሆነው ነበር፤ እኔም ጩኸታቸው አልተሰማኝም። ደስ የሚለው ነገር ፈረሱ ጉዳት አላደረሰብኝም፤ ይሁንና ይህ አጋጣሚ፣ መስማት እንደማልችል ቤተሰቦቼ እንዲያውቁ መንገድ ከፈተ።

ከዚያ በኋላ አንድ የቤተሰባችን ወዳጅ፣ መስማት ከተሳናቸው ሌሎች ልጆች ጋር ትምህርቴን እንድከታተል ሐሳብ አቀረበ፤ ስለዚህ አጎቴ ኒክ በሳስከቱን፣ ሳስካችዋን በሚገኘው መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት አስመዘገበኝ። ቤተሰቦቼ ከሚኖሩበት አካባቢ በርካታ ሰዓታት ርቆ ወዳለ ቦታ ተዘዋወርኩ፤ በወቅቱ ገና የአምስት ዓመት ልጅ በመሆኔ በጣም ፈርቼ ነበር። ቤተሰቦቼን ለመጠየቅ መሄድ የምችለው በበዓላት ወቅት እንዲሁም ክረምት ላይ ትምህርት ቤት ሲዘጋ ብቻ ነበር። በጊዜ ሂደት የምልክት ቋንቋ የቻልኩ ሲሆን ከሌሎች ልጆችም ጋር ተግባብቼ መጫወት ቻልኩ።

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መማር

በ1939 የቤታችን ሁለተኛ ልጅ የሆነችው ሜርየን ከቢል ዳንየልቸክ ጋር ትዳር መሠረተች፤ ከዚያ በኋላ እኔንና ሌላዋን እህቴን ፍራንሲስን ወደ ቤታቸው ወሰዱን። ከቤተሰባችን መካከል ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት እህቴ ሜርየንና ባሏ ነበሩ። ክረምት ላይ ትምህርት ቤት ተዘግቶ ወደ ቤት ስመለስ፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚማሩትን ነገር ለእኔ ለማካፈል የሚችሉትን ያህል ይጥሩ ነበር። እውነቱን ለመናገር፣ የምልክት ቋንቋ ስለማይችሉ ከእነሱ ጋር መግባባት ቀላል አልነበረም። ይሁንና ለመንፈሳዊ ነገሮች ፍቅር እንዳለኝ አስተውለው ነበር። እኔም ብሆን ሕይወታቸውን የሚመሩበት መንገድ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚለው ጋር እንደሚስማማ ተረድቼ ነበር፤ ስለሆነም አብሬያቸው መስበክ ጀመርኩ። ብዙም ሳይቆይ ለመጠመቅ ፍላጎት አደረብኝ፤ ስለዚህ መስከረም 5, 1941 ከጉድጓድ በወጣ ውኃ በተሞላ አንድ የብረት በርሜል ውስጥ ቢል አጠመቀኝ። ውኃው እጅግ በጣም ቀዝቃዛ ነበር!

መስማት ከተሳናቸው ሰዎች ጋር፣ በ1946 በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ

በ1946 ክረምት ላይ ወደ ቤት ስመለስ በክሊቭላንድ፣ ኦሃዮ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኘን። በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን፣ ፕሮግራሙን መከታተል እንድችል እህቶቼ እየጻፉ ያሳዩኝ ነበር። በቀጣዩ ቀን ግን በስብሰባው ላይ የምልክት ቋንቋ ቡድን እንዳለና ትምህርቱም ወደ ምልክት ቋንቋ እንደሚተረጎም በመስማቴ በጣም ተደሰትኩ። በመጨረሻም ከፕሮግራሙ ጥቅም ማግኘት የቻልኩ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በግልጽ መረዳት በመቻሌ በደስታ ፈነደቅኩ!

እውነትን ማስተማር

በዚያ ወቅት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ገና ማብቃቱ ስለነበር ብሔራዊ ስሜት እንደተጋጋለ ነበር። ከዚያ ትልቅ ስብሰባ ስመለስ፣ ከይሖዋ ጎን ለመቆም ቆርጬ ነበር። በመሆኑም በባንዲራ ሥነ ሥርዓት ላይ መካፈሌንና በምልክት ቋንቋ ብሔራዊ መዝሙር መዘመሬን አቆምኩ። በተጨማሪም በበዓላት እንዲሁም ግዴታ በነበረው የቤተ ክርስቲያን ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘት ተውኩ። ይህን ማድረጌ የትምህርት ቤቱን ሠራተኞች አላስደሰተም፤ እንዲያውም በማስፈራራትና በማታለል ሐሳቤን ሊያስቀይሩኝ ሞክረው ነበር። ሁኔታው አብረውኝ ይማሩ በነበሩት ተማሪዎች ላይ ግራ መጋባትን ፈጠረ፤ ለእኔ ግን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችል አጋጣሚ ከፍቶልኛል። ከእነዚህ መካከል ላሪ አንድሮሶፍ፣ ኖርማን ዲትሪክ እንዲሁም ኤሚል ሽናይደር የተባሉት ተማሪዎች እውነትን የተቀበሉ ሲሆን አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው።

ወደ ሌሎች ከተሞች ስሄድ መስማት ለተሳናቸው ሰዎች ለመመሥከር ሁልጊዜም ጥረት አደርጋለሁ። ለምሳሌ ሞንትሪያል ውስጥ፣ መስማት የተሳናቸው አንድ ማኅበር አባል ለሆነ ኤዲ ታገር ለተባለ ወጣት መሥክሬለት ነበር። ኤዲ ባለፈው ዓመት በሞት እስካንቀላፋበት ጊዜ ድረስ በላቫል፣ ኩዊቤክ ባለ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ አገልግሏል። ሁዋን አርዳኖዝ የተባለ ሌላ ወጣትም አግኝቼ ነበር፤ ሁዋን ልክ እንደ ቤርያ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ትክክል ስለመሆኑ በትጋት ምርምር ያደርግ ነበር። (ሥራ 17:10, 11) እሱም እውነትን የተቀበለ ሲሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በኦታዋ፣ ኦንታሪዮ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በታማኝነት አገልግሏል።

በ1950ዎቹ በመንገድ ላይ ስመሠክር

በ1950 ወደ ቫንኩቨር ተዛወርኩ። መስማት ለተሳናቸው ሰዎች መመሥከር ቢያስደስተኝም፣ ክሪስ ስፓይሰር ከተባለች መስማት የምትችል ሴት ጋር በተያያዘ ያጋጠመኝን ሁኔታ መቼም ቢሆን አልረሳውም፤ ለዚህች ሴት የመሠከርኩላት መንገድ ላይ ነበር። ሴትየዋ የመጽሔት ኮንትራት የገባች ሲሆን ከባለቤቷ ከጋሪ ጋር እንድገናኝ ፈልጋ ነበር። ስለዚህ ወደ ቤታቸው ሄድኩና በማስታወሻ ላይ እየተጻጻፍን ሰፋ ያለ ውይይት አደረግን። ከዚያ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት አልተገናኘንም፤ ይሁን እንጂ በቶሮንቶ፣ ኦንታሪዮ ባደረግነው ትልቅ ስብሰባ ላይ አግኝተው ሲያናግሩኝ በጣም ተገረምኩ። በዚያው ቀን ጋሪ ይጠመቅ ነበር። ይህ አስደሳች ተሞክሮ ምንጊዜም የመስበክን አስፈላጊነት አስገንዝቦኛል፤ ምክንያቱም እውነት በማን ልብ ውስጥ ወይም መቼ ሥር ሊሰድ እንደሚችል ማናችንም አናውቅም።

ከጊዜ በኋላ ወደ ሳስከቱን ተመለስኩ። በዚያም አንዲት እናት፣ ጂን እና ጆአን ሮተንበርገር የተባሉ መስማት የተሳናቸው መንትያ ልጆቿን መጽሐፍ ቅዱስ እንዳስጠናላት ጠየቀችኝ፤ እነዚህ እህትማማቾች የሚማሩት እኔ በተማርኩበት መስማት ለተሳናቸው የተዘጋጀ ትምህርት ቤት ውስጥ ነበር። ብዙም ሳይቆይ እህትማማቾቹ እየተማሩት ያለውን ነገር ለክፍል ጓደኞቻቸው ያካፍሉ ጀመሩ። ከጊዜ በኋላ አምስት የክፍል ጓደኞቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ከእነዚህ መካከል ዩነስ ኮለን ትገኝበታለች። ከዩነስ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው በዚያው ትምህርት ቤት የመጨረሻ ዓመት ተማሪ እያለሁ ነበር። በዚያ ወቅት ዩነስ ከረሜላ ከሰጠችኝ በኋላ ጓደኞች መሆን እንችል እንደሆነ ጠይቃኝ ነበር። ከጊዜ በኋላ ዩነስ የትዳር ጓደኛዬ በመሆኗ በሕይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላት ሰው ሆናለች!

ከዩነስ ጋር በ1960 እና በ1989

የዩነስ እናት፣ ልጇ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠናች እንዳለ ስታውቅ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪ አቋሟን ለማስቀየር እንዲሞክር አደረገች። አስተዳዳሪው ለማጥናት የሚረዷትን ጽሑፎች እንኳ ወሰደባት። ዩነስ ግን ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ቆርጣ ነበር። ለመጠመቅ እንደምትፈልግ ስትገልጽ ወላጆቿ “የይሖዋ ምሥክር ከሆንሽ ቤታችንን ለቀሽ ትወጫለሽ!” ብለዋት ነበር። ዩነስ በ17 ዓመቷ ከቤት የወጣች ሲሆን በአካባቢው የነበረ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ በደግነት ተቀበላት። በጥናቷ በመቀጠል ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ተጠመቀች። በ1960 ከዩነስ ጋር ስንጋባ ወላጆቿ በጋብቻ ሥነ ሥርዓታችን ላይ አልተገኙም። ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ግን በእምነታችንና ልጆቻችንን ባሳደግንበት መንገድ የተነሳ ለእኛ ያላቸው አክብሮት ጨምሯል።

ይሖዋ ተንከባክቦኛል

ልጄ ኒኮላስና ባለቤቱ ዴብራ በለንደን ቤቴል ያገለግላሉ

እኔና ዩነስ መስማት የተሳነን ብንሆንም ሰባቱ ልጆቻችን መስማት ይችላሉ። ልጆቻችንን ማሳደግ ተፈታታኝ ነበር፤ ሆኖም ከልጆቻችን ጋር በደንብ መግባባትና እውነትን ለእነሱ ማስተማር እንድንችል ልጆቻችን የምልክት ቋንቋ እንዲማሩ አድርገናል። በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶችም ቢሆኑ ትልቅ እገዛ አድርገውልናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ወላጅ ከልጆቻችን መካከል አንዱ በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ መጥፎ ቃላትን እንደሚናገር የሚገልጽ ማስታወሻ ጽፎ ሰጥቶን ነበር። በመሆኑም ሁኔታውን ለማስተካከል ወዲያውኑ እርምጃ መውሰድ ችለናል። አራት ወንዶች ልጆቼ ማለትም ጄምስ፣ ጄሪ፣ ኒኮላስ እንዲሁም ስቲቨን ከቤተሰባቸው ጋር ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ ነው። አራቱም ወንዶች ልጆቼ የጉባኤ ሽማግሌዎች ናቸው። በተጨማሪም ኒኮላስና ባለቤቱ ዴብራ በብሪታንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ባለው የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን ውስጥ ያገለግላሉ፤ ስቲቨንና ባለቤቱ ሻነን ደግሞ በዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ባለ የምልክት ቋንቋ ትርጉም ቡድን ውስጥ ያገለግላሉ።

ጄምስ፣ ጄሪና ስቲቨን የተባሉት ወንዶች ልጆቼ ከሚስቶቻቸው ጋር በመሆን በምልክት ቋንቋ የሚካሄደውን የስብከት ሥራ በተለያየ መንገድ ይደግፋሉ

ለ40ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላችን አንድ ወር ሲቀረን ዩነስ በካንሰር ምክንያት ሕይወቷ አለፈ። ከካንሰር ጋር ለረጅም ጊዜ በታገለችበት በዚያ አስቸጋሪ ወቅትም እንኳ ተስፋ አልቆረጠችም። በትንሣኤ ተስፋ ላይ የነበራት እምነት ኃይል ሰጥቷት ነበር። ዳግም እሷን የማገኝበትን ጊዜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ።

ፌይ እና ጄምስ፣ ጄሪ እና ኤቭሊን፣ ሻነን እና ስቲቨን

በሚያዝያ 2012 ወድቄ ወገቤ ላይ ጉዳት ደረሰብኝ፤ በዚህም ምክንያት የሌሎች እንክብካቤ አስፈለገኝ። በመሆኑም ከአንዱ ወንድ ልጄና ከባለቤቱ ጋር መኖር ጀመርኩ። አሁን በካልጋሪ የምልክት ቋንቋ ጉባኤ የምንሰበሰብ ሲሆን እኔም ሽማግሌ ሆኜ ማገልገሌን ቀጥያለሁ። የሚገርመው በምልክት ቋንቋ ጉባኤ ውስጥ ሳገለግል ይህ የመጀመሪያዬ ነው! ከ1946 አንስቶ ባሉት ዓመታት ሁሉ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ ውስጥ እያገለገልኩ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆኜ መቀጠል የቻልኩት እንዴት ነው? ይሖዋ፣ አባት የሌላቸውን ልጆች እንደሚረዳ የገባውን ቃል ስለ ጠበቀ ነው። (መዝ. 10:14) ማስታወሻ በመጻፍ፣ የምልክት ቋንቋን በመማር እንዲሁም አቅማቸው በፈቀደ መጠን ለእኔ ለማስተርጎም ጥረት ላደረጉ ሁሉ በጣም አመስጋኝ ነኝ።

በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በተካሄደ የአቅኚዎች ትምህርት ቤት በ79 ዓመቴ ስካፈል

እውነቱን ለመናገር፣ የሚተላለፈውን መልእክት መረዳት ስላልቻልኩ ወይም መስማት የተሳናቸው ሰዎች ምን እንደሚያስፈልጋቸው የሚረዳ ሰው እንደሌለ ሆኖ ስለተሰማኝ ያዘንኩባቸውና ተስፋ የቆረጥኩባቸው ጊዜያት ነበሩ። ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት ጴጥሮስ ለኢየሱስ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት የተናገራቸውን ቃላት አስታውስ ነበር። (ዮሐ. 6:66-68) በእኔ ዕድሜ እንዳሉ መስማት የተሳናቸው በርካታ ወንድሞችና እህቶች ሁሉ እኔም ትዕግሥትን መማር ነበረብኝ። ይሖዋንና ድርጅቱን መጠባበቅ እንዳለብኝ ተምሬያለሁ፤ ደግሞም ይህን በማድረጌ በጣም ተጠቅሜያለሁ! አሁን በቋንቋዬ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይገኛል፤ በአሜሪካ የምልክት ቋንቋ በሚመሩ የጉባኤ እና ትላልቅ ስብሰባዎች ላይም መገኘት እችላለሁ። በእርግጥም ታላቁን አምላካችንን ይሖዋን በማገልገል አስደሳችና የሚክስ ሕይወት መርቻለሁ።