ሥነ ምግባር በድንገት ማሽቆልቆል የጀመረበት ጊዜ
ሥነ ምግባር በድንገት ማሽቆልቆል የጀመረበት ጊዜ
ሥነ ምግባር ድንገት ያሽቆለቆለው ከመቼ ጀምሮ ነው ትላለህ? በአንተ ዕድሜ ነው ወይስ ከአንተ በሚበልጡ ዘመዶችህና ጓደኞችህ ዕድሜ? አንዳንዶች በ1914 የፈነዳው አንደኛው የዓለም ጦርነት ተወዳዳሪ የሌለውን የዘመናችንን የሥነ ምግባር ውድቀት እንዳስከተለ ይናገራሉ። ሮበርት ቮል የተባሉ የታሪክ ፕሮፌሰር ዘ ጀነሬሽን ኦቭ 1914 (የ1914 ትውልድ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ “ጦርነቱን የተመለከቱ ሰዎች ነሐሴ 1914 ላይ አንድ ዓለም አክትሞ ሌላ ዓለም መጀመሩን በሚገባ ያምናሉ” ብለዋል።
ታሪክ ጸሐፊው ኖርማን ካንተር እንዲህ ብለዋል:- “ቀድሞውንም ቢሆን በማሽቆልቆል ላይ የነበረው የኅብረተሰቡ ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ በሁሉም ሥፍራ ጭራሹኑ ተንኮታኩቷል። ፖለቲከኞችና ጀነራሎች በሥራቸው ያሉትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለዕርድ እንደሚነዱ እንስሳት የሚቆጥሯቸው ከሆነ ሰዎቹ እርስ በርሳቸው በዱር እንዳሉ አስፈሪ አራዊት እንዳይተያዩ የትኛው ሃይማኖታዊ ወይም ሥነ ምግባራዊ ደንብ ያግዳቸዋል? . . . ደም አፋሳሽ የነበረው አንደኛው የዓለም ጦርነት [1914-18] የሰውን ሕይወት ዋጋ አሳጥቶታል።”
እንግሊዛዊው ታሪክ ጸሐፊ ኤች ጂ ዌልስ ዚ አውትላይን ኦቭ ሂስትሪ በተሰኘው ሰፊ ርዕሰ ጉዳዮችን ባካተተው የጽሑፍ ሥራቸው ላይ “ሥነ ምግባር መበላሸት የጀመረው” የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ እንደሆነ ገልጸዋል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? አንዳንዶች ሰው ትንሽ ሻል ያለ እንስሳ እንደሆነ አድርገው ማሰብ ጀመሩ። እነዚህን ሰዎች በተመለከተም የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ አራማጅ የነበሩት ዌልስ በ1920 እንደሚከተለው ብለው ጽፈው ነበር:- “በኅብረት እንደሚያድኑት እንደ ሕንድ አዳኝ ውሾች ሁሉ ሰውም እየተረዳዳ የሚኖር እንስሳ ነው የሚል ውሳኔ ላይ ስለደረሱ . . . ብርቱዎቹ ደካሞቹን በኃይል መግዛታቸው ትክክል እንደሆነ ተሰማቸው።”
በእርግጥም ካንተር እንደገለጹት የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ሰዎች ለሥነ ምግባር በነበራቸው አመለካከት ላይ ጎጂ ውጤት አስከትሏል። እንዲህ ብለው ነበር:- “የቀድሞው ትውልድ በማንኛውም ነገር ለምሳሌ ያህል በፖለቲካዊ አቋሙ፣ በአለባበሱና ስለ ወሲብ ባለው አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተወቃሽ ነው።” የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ በመደገፍና ተፋላሚ ጎራዎችን በማበረታታት የክርስቲያናዊ ትምህርቶችን ስም ያጎደፉት አብያተ ክርስቲያናትም ለሥነ ምግባር ውድቀት ትልቅ ምክንያት ሆነዋል። ብሪታንያዊው ብርጋዴር ጀነራል ፍራንክ ክሮዜር “አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች ደም የማፍሰስ ጥማት እንዲያድርባቸው ለመቀስቀስ የምንጠቀምባቸው ዓይነተኛ መሣሪያዎቻችን ሲሆኑ እንደ ልባችንም ተጠቅመንባቸዋል” በማለት ጽፈዋል።
የሥነ ምግባር ደንቦች ገሸሽ ተደረጉ
ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በነበሩት አሥር ዓመታት ውስጥ የቀድሞዎቹ ማኅበራዊ እሴቶችና ሥነ ምግባራዊ ደንቦች ነውር የሚባል ነገር የለም በሚል አስተሳሰብ ተተኩ። ታሪክ ጸሐፊው ፍሬድሪክ ሎወስ አለን እንዲህ የሚል አስተያየት ሰጥተዋል:- “ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የነበሩት አሥር ዓመታት መጥፎ ምግባር የነገሠባቸው ዓመታት ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ። . . . ሕይወት ጣዕምና ትርጉም ያለው እንዲሆን የሚያደርጉ ማኅበራዊ እሴቶች የነበሩት አሮጌው ሥርዓት ሲያከትም ምትክ የሚሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በቀላሉ ማግኘት አልተቻለም።”
በ1930ዎቹ ዓመታት የተከሰተው ታላቁ የኢኮኖሚ ቀውስ ሰዎችን ለከፋ ድህነት ስለዳረጋቸው ብዙዎች ጭምቶች ሆኑ። ይሁን እንጂ በዚህ አሥር ዓመት ማብቂያ ላይ ዓለም ይበልጥ አውዳሚ ወደሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ውስጥ ገባች። ብዙም ሳይቆይ መንግሥታት አስፈሪ የሆኑ አጥፊ መሣሪያዎችን መሥራት መጀመራቸው ዓለም ከገባችበት የኢኮኖሚ ማጥ ውስጥ እንድትወጣ ቢያስችላትም ጦርነቱ ግን ለማሰብ የሚከብድ መከራና ሥቃይ አስከትሎባታል። ጦርነቱ በተጠናቀቀበት ወቅት በመቶዎች የሚቆጠሩ ከተሞች የፍርስራሽ ክምር ሆነው ነበር፤ ሁለት የጃፓን ከተሞች ደግሞ በየተራ በተጣለባቸው የአቶሚክ ቦምብ እንዳልነበሩ ሆኑ! በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች አሰቃቂ በሆኑ የማጎሪያ ካምፖች ውስጥ ለሕልፈት ተዳረጉ። ይህ ጦርነት በአጠቃላይ 50 ሚሊዮን የሚያክሉ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ሕይወት ቀጥፏል።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተካሄደባቸው በእነዚያ ቀውጢ ዓመታት ሰዎች ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፉ የቆዩትን መሥፈርቶች ከመከተል ይልቅ የራሳቸውን ደንብ አወጡ። ላቭ፣ ሴክስ ኤንድ ዋር—ቼንጂንግ ቫልዩስ፣ 1939-45 የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል:- “ጦርነቱ በቆየባቸው ዓመታት ጦር ሜዳ ላይ የነበረው አመለካከት ወደ ቤትም በመዛመቱ ሰዎች በወሲብ ረገድ ስሜታቸውን መግታት ያቆሙ ይመስል ነበር። . . . ጦርነቱ በፈጠረው የውክቢያና የጥድፊያ ስሜት ሳቢያ የሥነ ምግባር ደንቦች ስለላሉ የሲቪሉ ኅብረተሰብ ሕይወት በጦር ግንባር እንደነበረው ሁሉ ርካሽና አጭር እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።”
ከዛሬ ነገ እሞታለሁ የሚለው ስጋት ሰዎች ለአጭር ጊዜም ቢሆን ጾታዊ ቅርርብ እንዲመሠርቱ ገፋፋቸው። አንዲት ብሪታንያዊት የቤት እመቤት በእነዚያ ቀውጢ ዓመታት ሰዎች ለምን ልቅ እንደሆኑ ሰበብ ስታቀርብ “በእርግጥ ሥነ ምግባር የጎደለን ሰዎች ስለሆንን ሳይሆን በጦርነት ላይ ስለነበርን ነው” ብላለች። አንድ አሜሪካዊ ወታደርም “በብዙዎቹ መሥፈርት ከተመዘንን ሥነ ምግባር የጎደለን ሰዎች ነበርን፤ ይሁን እንጂ ወጣቶች የነበርን ከመሆኑም በላይ ነገ ልንሞት እንደምንችል እናውቃለን” በማለት ተናግሯል።
ከዚያ ጦርነት በሕይወት የተረፉ ብዙ ሰዎች በጦርነቱ ወቅት ያዩት ዘግናኝ ሁኔታ የስሜት ሥቃይ አስከትሎባቸዋል። በዚያን ጊዜ ሕፃናት የነበሩትን ጨምሮ አንዳንዶቹ የድሮው ነገር ትዝ ሲላቸው አሁንም እየተፈጸመ ያለ እየመሰላቸው ይዘገንናቸዋል። ብዙዎቹ እምነታቸው ጠፍቷል፤ እንዲሁም የሥነ ምግባር አቋማቸው ተዛብቶባቸዋል። ሰዎች ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር ደንብ ለሚያወጣ ለማንኛውም አካል የነበራቸው አክብሮት ስለጠፋ ነገሮች ሁሉ ከሁኔታዎች አንጻር መታየት ይኖርባቸዋል የሚል አቋም መያዝ ጀመሩ።
አዳዲስ ማኅበራዊ ደንቦች
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰውን ወሲባዊ ባሕርይ አስመልክቶ የተደረጉ አንዳንድ የጥናት ውጤቶች ለሕትመት መብቃት ጀመሩ። ከእነዚህ የጥናት ውጤቶች መካከል ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ1940ዎቹ ዓመታት ለሕዝብ ይፋ የሆነውና ከ800 በላይ ገጾች ያሉት የኪንሴ ሪፖርት ይገኝበታል። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ስለ ወሲባዊ ጉዳዮች ከዚያ በፊት ተደርጎ በማያውቅ መጠን በግልጽ መነጋገር ጀመሩ። ሪፖርቱ ግብረ ሰዶማዊነትንና ከተፈጥሮ ውጪ የሆኑ ሌሎች ወሲባዊ ድርጊቶችን በሚመለከት ያወጣቸው አኃዛዊ መረጃዎች የኋላ ኋላ እንደተጋነኑ ተደርገው ቢታዩም ጥናቱ፣ ጦርነቱን ተከትሎ የሰዎች ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ በሚያስገርም መንገድ ማሽቆልቆሉን ግልጽ አድርጓል።
ለተወሰኑ ጊዜያት ሥነ ምግባርን ጠብቆ ለማቆየት ጥረት ተደርጎ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በሬዲዮ፣ በተንቀሳቃሽ ፊልሞችና በቴሌቪዥን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆነ ይዘት ያለው ነገር እንዳይቀርብ ሳንሱር ይደረግ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ለረዥም ጊዜ አልዘለቀም። የዩናይትድ ስቴትስ የትምህርት ሚኒስቴር ጸሐፊ የነበሩት ዊልያም ቤኔት “በ1960ዎቹ ዓመታት አሜሪካ ከሥልጣኔ የኋሊት ጉዞ ጀምራ ነበር ለማለት ይቻላል” በማለት ገልጸዋል። ይህ ደግሞ በሌሎች በርካታ አገሮች ላይ ተጽዕኖ አድርጓል። በ1960ዎቹ ዓመታት የሰዎች ሥነ ምግባራዊ ሁኔታ ይበልጥ ያሽቆለቆለው ለምንድን ነው?
እነዚህ ዓመታት የሴቶች ነጻነት ንቅናቄና እንደ አዲስ የሥነ ምግባር ደንብ ይታይ የነበረው የጾታ አብዮት በአንድነት የተስተናገዱባቸው ዓመታት ነበሩ። በተጨማሪም ውጤታማ የሆኑ የወሊድ መቆጣጠሪያ ኪኒኖች በጥቅም ላይ ውለው ነበር። ይህ ደግሞ እርግዝና ይፈጠር ይሆናል የሚለውን ስጋት ስላስወገደው “በቃል ኪዳን መተሳሰር ሳያስፈልግ የፆታ ግንኙነት መፈጸም” የተለመደ እየሆነ መጣ።
በሌላ በኩል ጋዜጦች፣ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ሥነ ምግባርን በተመለከተ የነበራቸው አቋም መላላት ጀመረ። ዝቢግንዬቭ ብራዢንስኪ የተባሉ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ኃላፊ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የሚያንጸባርቁትን የሥነ ምግባር አቋም በተመለከተ ሲናገሩ “ሰዎች ለራሳቸው እርካታ እንዲቆሙ በግልጽ ያስተምራሉ፣ የዓመጽና የጭካኔ ድርጊቶች ምንም ችግር እንደሌለባቸው አድርገው ይናገራሉ እንዲሁም ልቅ የጾታ ግንኙነትን ያበረታታሉ” ብለዋል።
በ1970ዎቹ ዓመታት የቪዲዮ ማጫወቻዎች በሕዝብ ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈው ነበር። ሰዎች ቀደም ሲል ፊልም ቤቶች ውስጥ ማየት ያሳፍሯቸው የነበሩትን ከሥነ ምግባር ውጪ የሆኑና የፆታ ብልግናን በገሃድ የሚያሳዩ ፊልሞችን ቤታቸው መመልከት ጀመሩ። በቅርቡ ደግሞ በመላው ዓለም ኮምፒውተር ያላቸው ሁሉ ሊያዩት እንዲችሉ በኢንተርኔት አማካኝነት እጅግ አሳፋሪ የሆኑ እርቃንን የሚያሳዩ ወሲባዊ ምስሎች መቅረብ ጀምረዋል።
ይህ ሁኔታ የሚያስከትለው መዘዝ በብዙ መንገድ ሲታይ የሚያስፈራ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንድ የወኅኒ ቤት ኃላፊ ይህን በሚመለከት በቅርቡ እንዲህ ብለው ነበር:- “ከአሥር ዓመት በፊት ወጣቶች ወደ እስር ቤቱ ሲመጡ ትክክልና ስህተት ስለሆነ ነገር አነጋግራቸው ነበር። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ወደዚህ ለሚመጡ ልጆች ይህን ጉዳይ ሳነሳባቸው ስለምን እንደምናገር እንኳ አይገባቸውም።”
መመሪያ ከየት ማግኘት ይቻላል?
የሥነ ምግባር መመሪያዎችን በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት እናገኛለን ብለን መጠበቅ አይኖርብንም። ምክንያቱም እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት እንደ ኢየሱስና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት ተከታዮቹ የጽድቅ ሕግጋትን ከማስተማር ይልቅ ራሳቸውን የዚህ ዓለም ክፍል በማድረግ ወደ ክፋት አዘንብለዋል። አንድ ጸሐፊ “ሁለቱም ጎራዎች አምላክ ከእነርሱ ጎን እንደሚሰለፍ ሳይናገሩ የተካሄደ ጦርነት አለ?” ሲሉ ጠይቀዋል። የኒው ዮርክ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ቄስ የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጠበቅን በተመለከተ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት ሲናገሩ “በዓለም ላይ ካሉ ድርጅቶች መካከል ወደ አውቶቡስ ለመግባት እንኳ ከሚጠየቀው ያነሰ መሥፈርት ያላት ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት” ብለዋል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ በከፍተኛ ሁኔታ በማሽቆልቆል ላይ የሚገኘው የዓለም ሥነ ምግባር በአፋጣኝ አንድ ዓይነት እርምጃ መወሰድ እንዳለበት ይጠቁማል። ይሁንና ይህ እርምጃ ምንድን ነው? ምን ዓይነት ለውጥ መደረግ ይኖርበታል? ይህን ለውጥ ማምጣት የሚችለው ማን ነው? እንዴትስ?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“ደም አፋሳሽ የነበረው አንደኛው የዓለም ጦርነት [1914-18] የሰውን ሕይወት ዋጋ አሳጥቶታል”
[በገጽ 6, 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወራዳ የሆኑ መዝናኛዎችን በቀላሉ ማግኘት ይቻላል