ምድር ትጠፋለች?

ምድር ትጠፋለች?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

 አትጠፋም። ምድር በእሳት ተቃጥላ አትጠፋም ወይም በሌላ ምድር አትተካም። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ምድርን የፈጠራት ለዘላለም እንደሆነ ይናገራል።

  •   “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።”—መዝሙር 37:29

  •   “[አምላክ] ምድርን በመሠረቶቿ ላይ መሠረታት፤ እሷም ለዘላለም ከቦታዋ አትናወጥም።”—መዝሙር 104:5

  •   “ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—መክብብ 1:4

  •   “[አምላክ] ምድርን የሠራትና ያበጃት፣ አጽንቶም የመሠረታት፣ መኖሪያ እንድትሆን እንጂ ለከንቱ [አይደለም]።”—ኢሳይያስ 45:18

የሰው ልጆች ምድርን ያጠፏት ይሆን?

 የሰው ልጆች በአካባቢ ብክለት፣ በጦርነት አሊያም በሌሎች መንገዶች ምድርን እንዲያጠፏት አምላክ አይፈቅድላቸውም። እንዲያውም አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [ያጠፋቸዋል]።” (ራእይ 11:18) ግን ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

 አምላክ፣ ምድርን በተገቢው መንገድ መያዝ ያልቻሉትን የሰው ልጆች መንግሥታት አስወግዶ ፍጹም የሆነ ሰማያዊ መንግሥት በቦታቸው እንዲተካ ያደርጋል። (ዳንኤል 2:44፤ ማቴዎስ 6:9, 10) የዚህ መንግሥት ንጉሥ የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የተፈጥሮ ኃይሎችን መቆጣጠር እንደሚችል አሳይቷል። (ማርቆስ 4:35-41) ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ስለሆነ ምድርንም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን የተፈጥሮ ኃይሎች ይቆጣጠራል። በምድር ላይ ያሉ ሁኔታዎች እንዲሻሻሉና እንዲስተካከሉ ያደርጋል፤ ይህም መላዋ ምድር የኤደን ገነት ዓይነት ቦታ እንድትሆን ያስችላል።—ማቴዎስ 19:28፤ ሉቃስ 23:43

መጽሐፍ ቅዱስ ምድር በእሳት እንደምትጠፋ ያስተምራል?

 አያስተምርም። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የመጣው 2 ጴጥሮስ 3:7ን በተሳሳተ መንገድ ከመረዳት ነው፤ ጥቅሱ “ሰማያትም ሆኑ ምድር ለእሳት . . . ተጠብቀው ይቆያሉ” ይላል። ሆኖም ይህን ጥቅስ በትክክል ለመረዳት የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች መመልከት ያስፈልገናል፦

  1.   መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማያት”፣ “ምድር” እንዲሁም “እሳት” የሚሉትን ቃላት የተለያዩ ነገሮችን ለማመልከት ይጠቀምባቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 11:1 “ምድር ሁሉ አንድ ቋንቋና ተመሳሳይ ቃላት ትጠቀም ነበር” ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ “ምድር” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሰው ልጆችን በአጠቃላይ ነው።

  2.   በ2 ጴጥሮስ 3:7 ዙሪያ ያለው ሐሳብ ሰማያት፣ ምድር እንዲሁም እሳት የሚሉት ቃላት ያላቸውን ትርጉም ለመረዳት ያስችላል። ቁጥር 5 እና 6 ይህ ትንቢት የሚፈጸምበትን ሁኔታ በኖኅ የጥፋት ውኃ ጊዜ ከነበረው ሁኔታ ጋር ያመሳስሉታል። በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም የጠፋ ቢሆንም ፕላኔታችን ግን አልጠፋችም። በዚያን ጊዜ የጠፋው “ምድር” የተባለው ዓመፀኛ የሆነው ማኅበረሰብ ነበር። (ዘፍጥረት 6:11) በዚያ ዘመን የነበሩት “ሰማያት” ይኸውም ማኅበረሰቡን ያስተዳድሩ የነበሩ ሰዎችም ጠፍተዋል። በመሆኑም በወቅቱ የጠፉት ክፉ ሰዎች እንጂ ምድር አልነበረችም። ኖኅና ቤተሰቡም ቢሆን በወቅቱ የነበረው ዓለም ሲጠፋ በሕይወት የተረፉ ሲሆን ከጥፋት ውኃው በኋላም ምድር ላይ ይኖሩ ነበር።—ዘፍጥረት 8:15-18

 በጥፋት ውኃው ጊዜ እንደሆነው ሁሉ በ2 ጴጥሮስ 3:7 ላይ የተገለጸው ‘እሳትም’ የሚያጠፋው ግዑዟን ምድር ሳይሆን በውስጧ ያሉትን ክፉ ሰዎች ነው። አምላክ ‘ጽድቅ የሚሰፍንበት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር’ እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። (2 ጴጥሮስ 3:13) ‘አዲሱ ምድር’ ማለትም አዲሱ ማኅበረሰብ ‘በአዲስ ሰማያት’ ይኸውም በአዲስ መንግሥት አገዛዝ ሥር ይተዳደራል። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ሰላም የሰፈነባት ገነት ትሆናለች።—ራእይ 21:1-4