የኢየሱስ መሥዋዕት “ለብዙዎች ቤዛ” የሆነው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
የኢየሱስ መሥዋዕት አምላክ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ለመታደግ ወይም ለማዳን ያደረገው ዝግጅት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ቤዛ ሆኖ እንደተከፈለ ይናገራል። (ኤፌሶን 1:7፤ 1 ጴጥሮስ 1:18, 19) በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት’ እንደሆነ ተናግሯል።—ማቴዎስ 20:28፣ አዲሱ መደበኛ ትርጉም
“ለብዙዎች ቤዛ” ያስፈለገው ለምንድን ነው?
የመጀመሪያው ሰው አዳም ምንም ኃጢአት የሌለበት ፍጹም ሰው ነበር። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የነበረው ቢሆንም የአምላክን ትእዛዝ ለመጣስ በመምረጡ ይህን መብት አጥቷል። (ዘፍጥረት 3:17-19) ልጆች ሲወልድ ደግሞ ኃጢአትን ለልጆቹ አወረሰ። (ሮም 5:12) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ አዳም ራሱንና ልጆቹን ለኃጢአትና ለሞት ባርነት ‘እንደሸጠ’ ይጠቁማል። (ሮም 7:14) የአዳም ልጆች በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ማናቸውም ቢሆኑ አዳም ያጣውን ነገር መልሰው ማግኘት አይችሉም።—መዝሙር 49:7, 8
የአዳም ዘሮች የገጠማቸው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ አምላክን አሳዝኖታል። (ዮሐንስ 3:16) ነገር ግን አምላክ ፍትሐዊ በመሆኑ ያለምንም አጥጋቢ ምክንያት ኃጢአታቸውን ችላ ብሎ ሊያልፍ ወይም ይቅር ሊል አይችልም። (መዝሙር 89:14፤ ሮም 3:23-26) አምላክ፣ ለሰው ልጆች ፍቅር ስላለው የኃጢአት ይቅርታ እንዲያገኙ ብቻ ሳይሆን ኃጢአታቸው እንዲወገድ የሚያስችል ሕጋዊ መሠረት ጥሏል። (ሮም 5:6-8) ይህ ሕጋዊ መሠረት ቤዛው ነው።
ቤዛው ሕጋዊ መሠረት ሆኖ የሚያገለግለው እንዴት ነው?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቤዛ” የሚለው ቃል የሚከተሉትን ሦስት ነጥቦች ያካትታል፦
የሚከፈል ዋጋ ነው።—ዘኁልቁ 3:46, 47
ነፃ ለማውጣት ወይም ለመዋጀት ያስችላል።—ዘፀአት 21:30
ከሚከፈልለት ነገር ዋጋ ጋር ተመጣጣኝ ነው። a
የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት እነዚህን ሦስት ነጥቦች የሚያሟላው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ዋጋ፦ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ‘በዋጋ እንደተገዙ’ ይናገራል። (1 ቆሮንቶስ 6:20፤ 7:23) ይህ ዋጋ የኢየሱስ ደም ሲሆን ኢየሱስ በደሙ “ከየነገዱ፣ ከየቋንቋው፣ ከየሕዝቡና ከየብሔሩ ሰዎችን ለአምላክ [ዋጅቷል]።”—ራእይ 5:8, 9
ነፃ ማውጣት፦ የኢየሱስ መሥዋዕት “በቤዛው [ከኃጢአት] ነፃ አውጥቶናል።”—1 ቆሮንቶስ 1:30፤ ቆላስይስ 1:14፤ ዕብራውያን 9:15
ተመጣጣኝ ዋጋ፦ ኢየሱስ ያቀረበው መሥዋዕት አዳም ካጣው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ጋር የሚመጣጠን ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:21, 22, 45, 46) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ ሁሉ በአንዱ ሰው [በኢየሱስ ክርስቶስ] መታዘዝም ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” (ሮም 5:19) ይህ ጥቅስ የአንድ ሰው ሞት ለብዙ ኃጢአተኞች ቤዛ የሚሆነው እንዴት እንደሆነ ያሳያል። እንዲያውም ሰዎች ከመሥዋዕቱ ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስፈልገውን እርምጃ እስከወሰዱ ድረስ የኢየሱስ መሥዋዕት “ለሁሉ ተመጣጣኝ ቤዛ” ይሆናል።—1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6
a በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቤዛ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት የተከፈለን ክፍያ ወይም ዋጋ ያመለክታሉ። ለምሳሌ ካፋር የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “መሸፈን” የሚል ትርጉም አለው፤ ይህ ቃል በዘፍጥረት 6:14 ላይ መርከቡ በቅጥራን እንደተሸፈነ ወይም እንደተለቀለቀ ለመግለጽ ተሠርቶበታል። አብዛኛውን ጊዜ ይህ ቃል ኃጢአትን መሸፈንን የሚያመለክት ነው። (መዝሙር 78:38፣ የግርጌ ማስታወሻ) ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያለው ኮፌር የሚለው ቃል አንድን ነገር ለመሸፈን ወይም ለመዋጀት የሚደረገውን ክፍያ ያመለክታል። (ዘፀአት 21:30) በተጨማሪም አብዛኛውን ጊዜ “ቤዛ” ተብሎ የሚተረጎመው ሊትሮን የሚለው የግሪክኛ ቃል “ለመዋጀት የሚከፈል ዋጋ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (ማቴዎስ 20:28፣ በሪቻርድ ፍራንሲስ ዌይማውዝ የተዘጋጀው ዘ ኒው ቴስታመንት ኢን ሞደርን ስፒች) የግሪክ ጸሐፊዎች ይህን አገላለጽ አንድን ምርኮኛ ወይም ባሪያ ነፃ ለማውጣት የሚከፈልን ዋጋ ለማመልከት ተጠቅመውበታል።
እነዚህንስ አይተሃቸዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ኢየሱስ ያድናል—እንዴት?
የኢየሱስ አማላጅነት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ለመዳን የሚያስፈልገው በኢየሱስ ማመን ብቻ ነው?
መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች
ኢየሱስ የሞተው ለምንድን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ የኢየሱስ ሞት ለሰው ልጆች ከፍተኛ ጥቅም እንዳስገኘ ይናገራል። ለመሆኑ የኢየሱስ ሞት ምን ጥቅም አስገኝቷል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው