ይሖዋ ማን ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ እንደምናገኘው ይሖዋ እውነተኛው አምላክና የሁሉም ነገር ፈጣሪ ነው። (ራእይ 4:11) ኢየሱስም ሆነ እንደ አብርሃምና ሙሴ ያሉ ነቢያት ይሖዋን አምልከዋል። (ዘፍጥረት 24:27፤ ዘፀአት 15:1, 2፤ ዮሐንስ 20:17) ይሖዋ የአንድ ብሔር ብቻ ሳይሆን ‘የመላው ምድር’ አምላክ ነው።—መዝሙር 47:2
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ የሚለው ስም አምላክ ብቻ የሚጠራበት ስም ነው። (ዘፀአት 3:15፤ መዝሙር 83:18) ይህ ስም፣ “መሆን” የሚል ትርጉም ካለው የዕብራይስጥ ግስ የተገኘ ሲሆን አንዳንድ ምሁራን የአምላክ ስም “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም እንዳለው ይናገራሉ። ይህ ፍቺ፣ ይሖዋ ፈጣሪ በመሆንና ዓላማው ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ የሚጫወተውን ሚና ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ስም ባለቤት ስለሆነው አካል በተለይም ደግሞ የእሱ ዋነኛ ባሕርይ ስለሆነው ስለ ፍቅሩ እንድናውቅ ይረዳናል።—ዘፀአት 34:5-7፤ ሉቃስ 6:35፤ 1 ዮሐንስ 4:8
በዕብራይስጥ የአምላክ ስም የሚጻፈው יהוה (የሐወሐ) በሚሉት ቴትራግራማተን ተብለው የሚጠሩ አራት ፊደላት ሲሆን የዚህ ስም የአማርኛ ትርጉም ይሖዋ ነው። በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የመለኮታዊው ስም ትክክለኛ አጠራር እንዴት እንደነበረ አይታወቅም። ነገር ግን ሰዎች በአማርኛ ቋንቋ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ “ይሖዋ” የሚለውን አጠራር ሲጠቀሙበት ቆይተዋል፤ ሌሎች ቋንቋዎችም ብዙ ጊዜ ሲሠራበት የነበረውን የስሙን አጠራር ተጠቅመዋል።
በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የአምላክ ስም አጠራር እንዴት እንደነበር የማይታወቀው ለምንድን ነው?
የጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የሚጻፈው ያለ አናባቢ ነበር። የቋንቋው ተናጋሪ በሚያነብበት ጊዜ ተገቢውን አናባቢ እያስገባ ያነብባል። ሆኖም የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት (“ብሉይ ኪዳን”) ተጽፈው ከተጠናቀቁ በኋላ አንዳንድ አይሁዳውያን ‘የአምላክን ስም መጥራት ተገቢ አይደለም’ የሚል አጉል እምነት አዳበሩ። በመሆኑም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው በሚያነብቡበት ጊዜ የአምላክን ስም የያዘ ጥቅስ ሲያጋጥማቸው “ጌታ” ወይም “አምላክ” በሚሉት ቃላት ይተኩት ነበር። ዘመናት እያለፉ ሲሄዱ ይህ አጉል እምነት በመስፋፋቱ የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር ቀስ በቀስ እየተረሳ ሄደ። a
አንዳንዶች የአምላክ ስም “ያህዌህ” ተብሎ መነበብ እንዳለበት ይሰማቸዋል፤ ሌሎች ደግሞ ከዚህ የተለዩ አጠራሮችን መጠቀም እንደሚገባ ይናገራሉ። የዘሌዋውያንን መጽሐፍ ግሪክኛ ትርጉም በከፊል የያዘው የሙት ባሕር ጥቅልል መለኮታዊውን ስም ያኦ በማለት በግሪክኛ ፊደላት ጽፎታል። የጥንቶቹ ግሪካውያን ጸሐፊዎች ከዚህ አጠራር ሌላ እንደ ያኤ፣ ያቤ እና ያኦአ ያሉ አማራጭ አጠራሮችም ትክክል እንደሆኑ ይገልጻሉ፤ ያም ሆነ ይህ በጥንቱ የዕብራይስጥ ቋንቋ የአምላክ ስም አጠራር እንዴት እንደነበር በውል ማወቅ አንችልም። b
ብዙዎች የአምላክን ስም በተመለከተ ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት
የተሳሳተ አመለካከት፦ “ይሖዋ” የሚለውን ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያስገቡት ይህን ስም የሚጠቀሙ ተርጓሚዎች ናቸው።
እውነታው፦ በአራቱ የዕብራይስጥ ፊደላት (ቴትራግራማተን) የተጻፈው የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 7,000 ጊዜ ገደማ ተጠቅሶ ይገኛል። c በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች የአምላክን ስም አውጥተው “ጌታ” እንደሚለው ባሉ የማዕረግ ስሞች ተክተውታል።
የተሳሳተ አመለካከት፦ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ የራሱ የሆነ የግል መጠሪያ አያስፈልገውም።
እውነታው፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን በመንፈሱ በመምራት ስሙን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺህ በሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ እንዲያሰፍሩ ያደረገው እንዲሁም እሱን የሚያመልኩ ሰዎች ስሙን እንዲጠቀሙ ያዘዘው አምላክ ራሱ ነው። (ኢሳይያስ 42:8፤ ኢዩኤል 2:32፤ ሚልክያስ 3:16፤ ሮም 10:13) እንዲያውም አንዳንድ የሐሰት ነቢያት፣ ሕዝቦቹ ስሙን እንዲረሱ ለማድረግ በመሞከራቸው አምላክ አውግዟቸዋል።—ኤርምያስ 23:27
የተሳሳተ አመለካከት፦ አይሁዳውያን ይከተሉት በነበረው ወግ መሠረት የአምላክ ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መውጣት አለበት።
እውነታው፦ አንዳንድ የአይሁድ ጸሐፍት መለኮታዊውን ስም ለመጥራት እምቢተኛ እንደነበሩ አይካድም። ሆኖም ስሙን ከመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂያቸው ውስጥ አላወጡትም። ያም ሆነ ይህ አምላክ ሰብዓዊ ወጎችን ለመከተል ስንል የእሱን ትእዛዛት እንድንጥስ አይፈልግም።—ማቴዎስ 15:1-3
የተሳሳተ አመለካከት፦ በዕብራይስጥ የአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር ስለማይታወቅ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ልንጠቀምበት አይገባም።
እውነታው፦ በዚህ አባባል መሠረት አምላክ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች ስሙን አንድ ዓይነት በሆነ መንገድ እንዲጠሩት ይፈልጋል ማለት ነው። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ቋንቋ ይናገሩ የነበሩ በጥንት ዘመን የኖሩ የአምላክ አገልጋዮች የተጸውኦ ስሞችን በተለያየ መንገድ ይጠሩ እንደነበር ይጠቁማል።
የእስራኤል መስፍን የነበረውን ኢያሱን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ዕብራይስጥ ተናጋሪ የሆኑ ክርስቲያኖች ስሙን የሚጠሩት የሆሹዋ ብለው ሲሆን ግሪክኛ ተናጋሪ የሆኑት ደግሞ የሶስ ይሉታል። የኢያሱ የዕብራይስጥ ስም ግሪክኛ አጠራር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሯል፤ ይህም ክርስቲያኖች የተጸውኦ ስሞችን በቋንቋቸው በተለመደው አጠራር የመጥራት ልማድ መከተላቸው ተቀባይነት ያለው አካሄድ እንደሆነ ያሳያል።—የሐዋርያት ሥራ 7:45፤ ዕብራውያን 4:8
የአምላክን ስም ከመተርጎም ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከአምላክ ስም ትክክለኛ አጠራር ይበልጥ ሊያሳስበን የሚገባው ይህ ስም በትክክለኛው ቦታ ላይ መስፈሩ ነው።
a ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፒዲያ በሁለተኛ እትሙ፣ ጥራዝ 14፣ ገጽ 883-884 ላይ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ግዞቱ ካበቃ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ያህዌህ የሚለው ስም እጅግ ቅዱስ እንደሆነ ተደርጎ መታየት ጀመረ፤ በመሆኑም ይህ ስም አዶናይ ወይም ኤሎሂም በሚሉት ቃላት ይተካ ጀመር።”
b ለበለጠ መረጃ መጽሐፍ ቅዱስ—አዲስ ዓለም ትርጉም ላይ የሚገኘውን “መለኮታዊው ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ” (ተጨማሪ መረጃ ሀ4) የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
c ቲኦሎጂካል ሌክሲከን ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት፣ ጥራዝ 2፣ ገጽ 523-524ን ተመልከት።
እነዚህንስ አይተሃቸዋል?
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው