የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን ያፈርሳሉ? ወይስ የቤተሰብ ትስስር እንዲጠናከር ይረዳሉ?
እኛ የይሖዋ ምሥክሮች በራሳችንም ሆነ በሌሎች ቤተሰቦች መካከል ያለው ትስስር እንዲጠናከር ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን። የቤተሰብ መሥራች ለሆነው አምላክ አክብሮት አለን። (ዘፍጥረት 2:21-24፤ ኤፌሶን 3:14, 15) በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ ሰዎች አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሰፈራቸውን መመሪያዎች በመማራቸው ጠንካራና ደስተኛ ቤተሰብ መመሥረት ችለዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቤተሰቦች ጠንካራ ትስስር እንዲኖራቸው የሚረዱት እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር በጥብቅ ለመከተል ጥረት እናደርጋለን፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን የተሻለ ባል፣ ሚስት እንዲሁም ወላጅ እንድንሆን ረድቶናል። (ምሳሌ 31:10-31፤ ኤፌሶን 5:22–6:4፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:8) የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሃይማኖት የሚለያዩ የቤተሰብ አባላት እንኳ ተስማምተው እንዲኖሩ ይረዳሉ። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) የይሖዋ ምሥክር የሆነ የትዳር ጓደኛ ያላቸው የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች የተናገሩትን ተመልከት፦
“ከተጋባን በኋላ ባሳለፍናቸው የመጀመሪያዎቹ ስድስት ዓመታት ውስጥ የትዳር ሕይወታችን በጭቅጭቅና በብስጭት የተሞላ ነበር። ኢቬቲ የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ግን ይበልጥ አፍቃሪና ትዕግሥተኛ መሆን ጀመረች። ያደረገችው ለውጥ ትዳራችንን ከመፍረስ ታድጎታል።”—ክላኡር፣ ከብራዚል
“ባለቤቴ ቻንሳ፣ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ተቃውሜው ነበር፤ ምክንያቱም የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን እንደሚያፈርሱ አስብ ነበር። ከዚያ ወዲህ ግን መጽሐፍ ቅዱስ የትዳር ሕይወታችንን እንዳሻሻለው ማስተዋል ችያለሁ።”—አግነስ፣ ከዛምቢያ
የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መከተል በሚከተሉት ነገሮች ረገድ እንዴት ሊጠቅማቸው እንደሚችል ለሰዎች እንናገራለን፦
የትዳር ጓደኛን ለመምረጥ
የመጀመሪያውን ዓመት የትዳር ሕይወት ስኬታማ ለማድረግ
ከአማቶች ጋር ተስማምቶ ለመኖር
የገንዘብ አያያዝ
ጭቅጭቅን ለማስወገድ
ሌሎችን ይቅር ለማለት
ልጆችን ለማሠልጠን
ሃይማኖትን መቀየር በትዳር ውስጥ ግጭት እንዲፈጠር ያደርጋል?
እውነት ነው፣ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሶፍር የተባለ ጥናት የሚያካሂድ አንድ ድርጅት በ1998 ያወጣው ሪፖርት እንደሚያሳየው አንዱ የትዳር አጋር ብቻ የይሖዋ ምሥክር ከሆነባቸው ከ20 ትዳሮች መካከል የትዳር አጋሩ የይሖዋ ምሥክር ለመሆን በመወሰኑ ምክንያት በአንዱ ትዳር ውስጥ ከባድ ችግር ተከስቶ ነበር።
ኢየሱስ፣ የእሱን ትምህርት የሚከተሉ ሰዎች አንዳንድ ጊዜ ቤተሰቦቻቸው ሊቃወሟቸው እንደሚችሉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:32-36) የታሪክ ምሁር የሆኑት ዊል ዱራንት፣ በጥንት ዘመን በሮም ግዛት ውስጥ “ክርስትና ቤተሰብን ያፈርሳል የሚል ክስ ተሰንዝሮበት” a እንደነበር ተናግረዋል፤ በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ክስ ቀርቦባቸዋል። እንዲህ ሲባል ታዲያ በትዳር ውስጥ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂው የይሖዋ ምሥክር የሆነው ወገን ነው ማለት ነው?
የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ‘የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብን ያፈርሳሉ’ ተብሎ ለቀረበባቸው ክስ ብይን በሰጠበት ወቅት እንደገለጸው ብዙውን ጊዜ ለግጭት መንስኤ የሚሆነው የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑት የቤተሰብ አባላት “ሌላኛው ወገን ሃይማኖቱን ለመከተል እና ለማራመድ ያለውን መብት አምነው ለመቀበልም ሆነ ለማክበር ፈቃደኛ አለመሆናቸው” ነው። አክሎም ፍርድ ቤቱ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ደግሞ አንደኛው ወገን የይሖዋ ምሥክር በሆነባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ ሃይማኖት በማይከተሉ ሌሎች ቤተሰቦች ውስጥም የሚያጋጥም የተለመደ ችግር ነው።” b የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው የተነሳ ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም እንኳ “ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ። . . . ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ለመከተል ይጥራሉ።—ሮም 12:17, 18
የይሖዋ ምሥክሮች የእነሱን ሃይማኖት ከማይከተል ሰው ጋር ትዳር መመሥረት የማይፈልጉት ለምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ክርስቲያኖች ማግባት ያለባቸው “በጌታ ብቻ” እንደሆነ ይኸውም የእነሱን እምነት ከሚጋራ ሰው ጋር ብቻ መጋባት እንዳለባቸው የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ይታዘዛሉ። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር መታዘዝ ጥቅም ያስገኛል። ለምሳሌ ያህል ጆርናል ኦቭ ሜሬጅ ኤንድ ፋሚሊ የተባለው መጽሔት በ2010 ባወጣው ጽሑፍ ላይ እንደገለጸው “የትዳር አጋሮች ተመሳሳይ ሃይማኖትና እምነት ካላቸው” ጥሩ ዝምድና የመመሥረት አጋጣሚያቸው የሰፋ ነው። c
ይሁን እንጂ የይሖዋ ምሥክሮች፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነ የትዳር ጓደኛ ያላቸው ሰዎች ከትዳር ጓደኛቸው እንዲለያዩ አያበረታቱም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “አንድ ወንድም አማኝ ያልሆነች ሚስት ካለችውና አብራው ለመኖር ከተስማማች አይተዋት፤ እንዲሁም አማኝ ያልሆነ ባል ያላት ሴት ባሏ አብሯት ለመኖር ከተስማማ አትተወው።” (1 ቆሮንቶስ 7:12, 13) የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ትእዛዝ ያከብራሉ።
ተዛማጅ ርዕሶች
ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎችእነዚህንስ አይተሃቸዋል?
ስለ እኛ
አንድ የይሖዋ ምሥክር መጥቶ እንዲያነጋግርህ ጠይቅ
ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስለምትፈልገው የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳይ መወያየት ወይም መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ከምናስተምርበት ዝግጅት መጠቀም ትችላለህ።
ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች